Skip to Content

ዜና

ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማዕከል ተመረቀ

‹‹የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስገነባው ግዙፍና ዘመናዊ ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማዕከል ከተሠራበት ቁስ በላይ ዓላማውና የያዘወው ማራኪ ሥነ ሕንጻ የቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚፈለገው ልክ የሚጠናከርበት፣ ለቀጣዩ ትውልድም የምናቆየው ዘመን ተሻጋሪ ሀብት ነው››

የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት / EOTC Broadcasting Service Agency · 12 Oct 2026 · 1 ደቂቃ ንባብ

ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማዕከል ተመረቀ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስገነባው ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማዕከል በተመረቀበት መርሐ ግብር ላይ ቃለ ቡራኬና በረከት አስተላልፈዋል።

‹‹የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ያስገነባው ግዙፍና ዘመናዊ ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማዕከል ከተሠራበት ቁስ በላይ ዓላማውና የያዘወው ማራኪ ሥነ ሕንጻ የቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚፈለገው ልክ የሚጠናከርበት፣ ለቀጣዩ ትውልድም የምናቆየው ዘመን ተሻጋሪ ሀብት ነው››

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያስገነባቸው ግዙፍ ዘመናዊና ሁለገብ ዓለም አቀፍ የጉባኤ ማእከል በተመረቀበት ደማቅ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት ቃለ ቡራኬና በረከት፡- ሕንጻው የቅዱስ ሲኖዶስ፥ የስብከተ ወንጌልና ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያትን ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችሉ አዳራሾች የተካተቱበት፣ ዋጋው በተሠራበት ቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን በተገነባበት ዓላማ ጭምር የሚለካና ልዩ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

ቅዱስነታቸው አያይዘውም ሕንጻው የቦታ አጠቃቀምንና ማራኪ ሥነ ሕንጻን በማዋሐድ ተገንብቶ መጠናቀቁን ጠቅሰው፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚፈለገው ልክ የሚጠናከርበትና ለቀጣዩ ትውልድም የምናቆየው ዘመን ተሻጋሪ ሀብት በመሆኑ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

የአዲሱ ሕንጻ የግንባታ ሐሳብ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፭ኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ መዋዕለ ሕይወት ተነሥቶ፤ ዕቅዱን የማደራጀትና የግንባታ ተግባሩ በየዘመነ ሢመታቸው ቤተ ክርስቲያንን የመሩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በኃላፊነትና በትጋት አሻራቸውን እያሳረፉበት እንዲሁም ብዙዎች በዕውቀታቸው፥ በጉልበታቸው እየተሳተፉበት ለዚህ በዘመን ደርሶ በልዩ ጥራት መጠናቀቁን ያበሰሩት ቅዱስነታቸው፤ በሥራ ላይ ለሚገኙት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፥ በየደረጃው ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ሓላፊዎች እንዲሁም ለሁሉም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመጨረሻም፤- በአዲሱ ጽርሐ ተዋሕዶ የሚደረጉ ጉባኤያት ሃይማኖትን ለማጽናት፥ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት፥ ለሕዝቡ ደኅንነትና ለሀገር ሰላም አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ፥ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ከነሙሉ ክብሩ ለትውልድ የሚሸጋገርባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ከአባታዊ አደራ ጋር አሳስበዋል።

የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት / EOTC Broadcasting Service Agency

ተዛማጅ

፵፭ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ  ጉባኤ

ዜና

፵፭ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፵፭ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ
በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክ ዐዲሱ የጽርሐ ተዋሕዶ የስብሰባ ማዕከል ከጥቅምት ፫ - ፯ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ
ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡

ዜና

ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡
መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተገነባው አዲሱ ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ሁለገብ የሰብሰባ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ማዕከል ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ሕንጻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡
ይህ ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ውበት የተላበሰው ሕንጻ በሚገባ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በሕንጻው ዙሪያ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንዲኖር፥ ቅጽረ ግቢው ቤተ ክርስቲያንን በሚገልጽ ሥነ ጥበብ እንዲያጌጥ ተደርጎ የተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በምሕንድስና ባለሙያዎቹ እንደተገለጸው ዓለም አቀፍ ሁለገብ ሕንጻ ከ2‚260 በላይ ተሰብሳቢዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዳራሽ፥ ሌሎች አነስተኛ የስብሰባና የሥልጠና አዳራሾች፣ ከአንድ መቶ በላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን የሚይዝ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ፥ ሙዚየምና ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ ቢሮዎች፣ ዘመናዊ ሬስቶራንትና ለሌሎችም አገልግሎት የሚሰጥ ክፍሎችን የያዘ ተገልጿል፡፡
አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጥቅምት ፩ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም የሚመረቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/ See less

ተጨማሪ ያንብቡ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መምሪያ የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ።

ዜና

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መምሪያ የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) መምሪያ የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ
ከአይሲቲና ዲጂታል ሽግግር አማካሪ ኮሚቴ ጋር ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የሥልጠና የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ ።
በሥልጠው የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የአይሲቲ ዋና ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተሳተፉ ሲሆን ፤ ሥልጠናው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቁትን የአይሲቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማስተዋወቅ፣ የሶፍትዌር ምንነት ለቤተክርስቲያኗ ዘመናዊ አሠራር ካለው ፋይዳ ጋር ማገናዘብ፣ እንዲሁም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂዎች በቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ላይ የሚፈጥሯቸውን ዕድሎችና ተግዳሮቶች መመርመር ዋና ዓላማዎቹ አድርጓል።
በሥልጠና መዝጊያ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም ዐሥራት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የኢንፎርሜሽን እና ኮሚንኬሽን የመምርያ ኃላፊ እና የድርጅት ኃላፊዎች ፣ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ የአማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ "ጥበብን ማግኘት ከወርቅ ይበልጣል" የሚለውን የመጽሐፍ ምሳሌ ኃሣብ በማንሳት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘመኑን መዋጀ አገልግሎት እንድትሰጥ የኢፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ሥልጠና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሥልጠናው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ለቤተክርስቲያን አገልግሎት፦ በወቅታዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ በተደረጉ ውይይቶችም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለዘመናዊ የሰነድ አያያዝ፣ ለፈጣን መረጃ ልውውጥ እና ለሰፊ ተደራሽነት ትልቅ ዕድል መሆኑ ተነስቷል። አጠቃቀሙም ለወደፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ለሚጸድቁ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ግብአት እንደሚሆን ተመላክቷል።
በሥልጠናው መርሐ ግብር ላይ በተለያዩ ምሁራን የቀረቡ ጥናቶች እና ሙያዊ ማብራሪያዎች ቀርበዋል።
በሥልጠናዎቹ ዙሪያ ሙያዊ ውይይት ተከናውኗል ።
በሥልጠናው መጨረሻ ቀሲስ ዮሐንስ ተስፋዬ በቀጣይ ትግበራ ላይ መመሪያ እና ኃሳብ ሰጥተዋል። የተግባር እቅድ ማውጣት፣ ያሉትን ክፍተቶች መሙላት፣ የመረጃ ጥራትን ማሻሻል፣ የአጠቃቀም መመሪያ ማውጣት፣ የደኅንነት ሥርዓት ማዘጋጀት፣ የሚድያ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የAI ስህተቶችን ማረም ፣ ክትትል እና ግምገማ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሥልጠናውን ተከትሎ ሁሉም ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት የሰለጠነና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

መጋቤ ጥበብ ሙሉዓለም ዐሥራት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ
ኃላፊነቱን ከተረከቡ ጀምሮ በአይሲቲው ዘርፍ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት በሰጡት መመሪያ መሠረት የቴክኖሎጂ ሥራዎች በጥንቃቄ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ተደርጓል ብለዋል።

አክለውም ለቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደራዊ ሥራዎች ፈተና እየሆኑ ባሉ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) እና የዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ የመነሻ ውይይቶች በማድረግ ለወደፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ለሚጸድቁ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ግብአት የሚሆኑ ሐሳቦች እንደሚሰባሰቡ አስረድተዋል፡፡ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) በአግባቡ ከተጠቀምንበት ትልቅ ዕድል ሲሆን፣ ካልሆነ ግን ተጓዳኝ ችግሮች ስለሚመጡ አጠቃቀሙን በጥንቃቄ መረዳት ያስፈልጋል። በመሆኑም ከሥልጠናው በኋላ ሁሉም ባለሙያና ኃላፊ ወደ ተግባር በመቀየር የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት የሰለጠነና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በመጨረሻም ለሥልጠናው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና እና በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ቡራኬ ፤ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል ።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/

ተጨማሪ ያንብቡ