Skip to Content

ዜና

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

የኢኦተቤ መገናኛ · 23 Oct 2026 · 2 ደቂቃ ንባብ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን፡፡
ብፁዕ ኣባ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣባ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፤
በኣጠቃላይ በዚህ ቅዱስና ሓዋርያዊ የሲኖዶስ ጉባኤ የተገኛችሁ ወገኖቻችን በሙሉ!
በቤቱ የታመን ሆነን ልናገለግል የመረጠንና በልዩ ኣጠራሩ የጠራን እግዚአብሔር ኣምላካችን ከየኣቅጣጫው ኣምጥቶ ኣንድ ላይ ስለ ሰበሰበን ክብርና ኣምልኮ ለእርሱ ይሁን! እናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ!
“ጻድቅ ወምእመን ለዘፈነዎ በከመ ሙሴ ውእቱሂ ላዕለ ኵሉ ቤቱ፡- ሙሴ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ እርሱም ለሾመው የታመነ ነበረ” (ዕብ ፫÷፪)፤
ቅዱስ መጽሓፍ በዚህ ዓረፍተ ነገር ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት መታመን ታላቅ የሹመት መስፈርት መሆኑን ነው፤
ቃሉ እውነትና የታመነ ነውና በእርግጥም ኃላፊነት ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት መታመን መሠረታዊ ነገር ነው፤
ኣለመታመንን በማይወድ ኣምላካችን ዘንድ ይቅርና፣ በዓመፀኛው ዓለምም ቢሆን መታመን ከሌለ ኃላፊነት ኣይሰጥም፤
እግዚአብሔር ሙሴን ለላቀ ኃላፊነት ሲመርጥ ታማኝ መሆኑን ኣይቶ ነው፤ በእርግጥም ሙሴ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ሕዝብ የታመነ ነበረ፤
ሙሴ የንጉሥ ልጅ ከመባል ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን፣ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍን፣ በኃጢኣት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ መሰደድን በመምረጥ ታማኝነቱን በተግባር ያረጋገጠ ነበር፤
በዚህም እግዚአብሔር ሙሴን ኣምኖ በሕዝቡ ላይ ሾሞታል፤ እሱም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ኃላፊነቱን ተወጥቶኣል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ኣስተምህሮ ሳይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች ኣሰራር ውሱን ሕፀፅ ባይጠፋም፣ መዓዛ መንፈስ ቅዱስ ኣይለያትምና ኣሁንም ዓለም መታመንን ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ትጠብቃለች፤
ከዚህ ኣኳያ ይህ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን መታመን እንዲኖር ኣብዝቶ የመስራትና የማሰራት ግዴታና መለኮታዊ ኃላፊነት ኣለበት፤
በዓለ መክሊቶቹ ‹‹ባእ ውስተ ፍሥሓሁ ለእግዚእከ›› ተብለው የተመሰገኑበትና የተሸለሙበት ዋና ምክንያት ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ የምናውቀውና በየቀኑ የምናነበው ነው፡፡
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
ጉባኤ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት የተሳሳተ ሲኖር ለማስተካከል፤ የተዛባ ሲኖር ለማቅናት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤
ከዚህ ኣንጻር በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሰው ኃይል ኣስተዳደራችን፣ የሃብት ኣጠባበቃችን እንዲሁም የምእመናን ኣያያዛችንና ሓዋርያዊ ተልእኮኣችን ለዘመኑ የማይመጥን እንደሆነ በስፋት እየተወሳ ነው፤
አስወቃሽ ምልክቶችም እየታዩ ነውና ያሉብንን የኣሰራር ክፍተቶችን በሚገባ ፈትሸን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘላቂ መፍትሔን በማስቀመጥ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት በተለይም በኣፍሪካና በላቲን ኣሜሪካ ያሉ ዕድሎችን በታቀደና በተጠናከረ ሁኔታ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ይህ ጉባኤ ማየት ኣለበት፣
ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተልእኮ በኣግባቡ መወጣት የሚችለው በሃገር ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሕዝባችን ካጋጠመው ያልተቋረጠ መከራና ጭንቀት ያርፍ ዘንድ፤ ለሰላም ከመጸለይ ባሻገር የማግባባት፣ የማስታረቅና የማስማማት ስራ ከኛ ይጠበቃልና በዚህም መወያየት ይኖርብናል፤ ለባለ ድርሻ ኣካላትም የሰላምን ጥሪ ማስተላለፍ ይገባናል፡፡
በመጨረሻም
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከጥቅምት ዓሥራ ሁለት ቀን ጀምሮ የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖደስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን ለኦርቶዶክስ ምእመናን እናበስራለን ፡፡
እግዚአብሔር የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!
ኣባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘኣኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ - ኢትዮጵያ

ተዛማጅ

የኀዘን መግለጫ|Message of Condolence

ዜና

የኀዘን መግለጫ|Message of Condolence

26 Oct 2026

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰጠ የኀዘን መግለጫ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአርሲ ዞን ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ/ም በመርቲ ወረዳ አንጋዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጎራ ሲሊንጎ 14 ምእመናን፣ በሸርካ ወረዳ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምእመናን ግፍን በተሞላ ጭካኔ ተገድለው ሕይወታቸው ማለፉን፣ የ20 ምእመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን፣ ከ20 በላይ የሆኑ ወገኖቻችን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል እንደሚገኙ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የቀረበውን ሪፖርት የሰማነው በከፍተኛ ኀዘን ነው፡፡ በአርሲ ሀገረ ስብከትና በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ንፁሐን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱና ከአሁን በፊትም በዞኑ ሥር በሚገኙ ወረዳዎች በርካታ ምእመናን መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን እጅግ አሳዛኝ ግፍና መከራ ጥልቅ በሆነ የኃዘን ስሜት ተመልክቶ እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በየትኛውም እምነት አስተምህሮም ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ የሃይማኖት ነፃነትና በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕገ ሰብእና የወጣ፣ ተከባብሮ የመኖር ሀገራዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጽኑ አውግዞታል፡፡ የንፁሐኑ ግድያ እንዲቆም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በይፋ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና በነጻነት የማምለክ መብትን እንዲያስከብሩልን፣ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ወንጀለኞችም ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ በደረሰው የልጆቻችን ሕልፈተ ሕይወት የተሰማንን ከፍተኛ ኃዘን በድጋሚ እየገለጽን፣ - ምእመናን ልጆቻችን በያሉበት ተመሳሳይ ጥቃት እንዲይደርስባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ፣ - የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ እንደመንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉና አደጋዎችን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ እያሳሰብን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን በመመኘት በግፍ ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ ዕረፍተ ነፍስንና ክብረ ሰማዕታትን እንዲያድልልን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አባላት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ፍትሐት እንዲፈጸም፣ ነገ ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ በመላው ዓለም በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት በሙሉ ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመለከተው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ቀጠሮ ተይዞለት ውይይት እንዲያደርግና በቀጣይም ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታት ጥናት የሚያደርጉ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንዲሰየም መመሪያ በመስጠት ተገቢው ጥረት እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ተጨማሪ ያንብቡ
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል

ዜና

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል

21 Oct 2026

የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡የብፁዕ ሊቀጳጳሱ ጸሎተ ፍትሐት ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ከቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ጋር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ መሪነት የሚከናወን ሲሆን ፤ የሌሊቱ ሥርዓተ ፍትሐት እና አደራረስ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቀጥሎ የሚከናወን ይሆናል፡፡የብፁዕ አቡነ ሉቃስ ግብአተ መሬት ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቅዳሴ በኋላ የሚፈጸም መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ
የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

ዜና

የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

19 Oct 2026

የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ። ዘጋቢ ሰላም አምባዬ (#EOTCTV ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለዘመናት ሲገነባ የቆየውን ''ጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል ተብሎ የተሰየመው ዘመናዊ የጉባኤ ማዕከል ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ተመርቋል። በምረቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዓለም ዓቀፉ የጉባኤ ማዕከል ግንባታ ለፍጻሜው ሊበቃ የቻለው በየዘመናቱ የተተኩ ቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ባደረጉት ያልተቋረጠ ክትትልና አባታዊ አመራር መሆኑን በሕንጻው ምርቃት ላይ በስፋት ተገልጿል ። በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ፣ ተቋማዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታስቦ የተገነባ ሲሆን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛና አስቸኳይ ጉባኤያትን፣ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን፣ የእህት አብያተ ክርስቲያናትንና የዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ተቋማት የጋራ ስብሰባዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳለው ገልጸዋል ። ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በንግግራቸው አዳራሹ ከስብሰባ አዳራሽነቱ ባሻገር ለልዩ ልዩ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች የሚውሉ ዘመናዊ ቢሮዎችን፣ ያካተተ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፤ ለተኪው ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ቅርስ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም አክለዋል ። በተጨማሪም የጉባኤው ማእከል ከስብሰባ አዳራሽነት ባሻገር ለልዩ መንፈሳዊ፥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች የሚውሉ ዘመናዊ ቢሮዎችን፥ አነስተኛ የስብሰባ ክፍሎች እና ጥናታዊ ሲምፖዚየሞች የሚካሄዱባቸውን መድረኮችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን ያካተተ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ። የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/ See less

ተጨማሪ ያንብቡ