ዜና
የቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ጸሎት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተካሄደ፡፡
የቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከብሯል፡፡ የቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ቀን ሥነ ሥርዐት ላይ በቁጥር በጣም አነስተኛ ሰው የተገኘበት ነበር፡፡ መጋቤ ካህናት መ/ር ዕንቁባሕርይ ተከስተ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ እንደተናገሩት “ዛሬ የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ቀን ሁሉም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተው ሊያከብሩት ይገባ” ነበር ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ቀን ላይ አነስተኛ ሰው መገኘቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ብፁዕነታቸው “ዛሬ የምናከብረው የአባቶቻችን መታሰቢያ ቀን ታቦት ወጥቶ ሊከበር ይገባ ነበር፣ ዛሬ ታቦት ይወጣል ቢባል ማንም ሰው አይቀርም ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት በአጠቃላይ ምእመናን ሊያከብሩት የሚገባ በዓል ነበር” በማለት በቁጥር በጣም አነስተኛ ሰው በመገኘቱ ተቆጭተው ተናግረዋል፡፡ “ዛሬ ያከበርነው የአባቶቻችን መታሰቢያ ቀን ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው አባቶቻችን የታሰሩበትን፣ የተገደሉበትን ታሪክ ማወቅ አለብን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ፤ የቤተክርስቲያንን አስተዳደር የበለጠ በማጠናከር ልዩ ልዩ ጠቃሚ ተግባራትን ያከናወኑትን፣ ሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋም ያደረጉትን በግፍ የገደሏቸው፡፡ ይህ ዛሬ ምን እንዳመጣ እያየን ነው አባቶቻችንን ማሩን ልንል ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በቀጣይ ዓመት እግዚአብሔር ካደረሰን ሁላችንም፣ ካህናትም፣ ወጣቶችም ተሰባስበን የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መታሰቢያ ቀን ልናከብር ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ምንጭ :- የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
ተጨማሪ ያንብቡ