ዜና
ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡
መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተገነባው አዲሱ ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ሁለገብ የሰብሰባ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ማዕከል ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ሕንጻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡
ይህ ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ውበት የተላበሰው ሕንጻ በሚገባ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በሕንጻው ዙሪያ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንዲኖር፥ ቅጽረ ግቢው ቤተ ክርስቲያንን በሚገልጽ ሥነ ጥበብ እንዲያጌጥ ተደርጎ የተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በምሕንድስና ባለሙያዎቹ እንደተገለጸው ዓለም አቀፍ ሁለገብ ሕንጻ ከ2‚260 በላይ ተሰብሳቢዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዳራሽ፥ ሌሎች አነስተኛ የስብሰባና የሥልጠና አዳራሾች፣ ከአንድ መቶ በላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን የሚይዝ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ፥ ሙዚየምና ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ ቢሮዎች፣ ዘመናዊ ሬስቶራንትና ለሌሎችም አገልግሎት የሚሰጥ ክፍሎችን የያዘ ተገልጿል፡፡
አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጥቅምት ፩ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም የሚመረቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/ See less