Skip to Content

ዜና

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

የኢኦተቤ መገናኛ · 23 Oct 2026 · 2 ደቂቃ ንባብ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን፡፡
ብፁዕ ኣባ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣባ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፤
በኣጠቃላይ በዚህ ቅዱስና ሓዋርያዊ የሲኖዶስ ጉባኤ የተገኛችሁ ወገኖቻችን በሙሉ!
በቤቱ የታመን ሆነን ልናገለግል የመረጠንና በልዩ ኣጠራሩ የጠራን እግዚአብሔር ኣምላካችን ከየኣቅጣጫው ኣምጥቶ ኣንድ ላይ ስለ ሰበሰበን ክብርና ኣምልኮ ለእርሱ ይሁን! እናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ!
“ጻድቅ ወምእመን ለዘፈነዎ በከመ ሙሴ ውእቱሂ ላዕለ ኵሉ ቤቱ፡- ሙሴ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ እርሱም ለሾመው የታመነ ነበረ” (ዕብ ፫÷፪)፤
ቅዱስ መጽሓፍ በዚህ ዓረፍተ ነገር ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት መታመን ታላቅ የሹመት መስፈርት መሆኑን ነው፤
ቃሉ እውነትና የታመነ ነውና በእርግጥም ኃላፊነት ለመቀበልም ሆነ ለመስጠት መታመን መሠረታዊ ነገር ነው፤
ኣለመታመንን በማይወድ ኣምላካችን ዘንድ ይቅርና፣ በዓመፀኛው ዓለምም ቢሆን መታመን ከሌለ ኃላፊነት ኣይሰጥም፤
እግዚአብሔር ሙሴን ለላቀ ኃላፊነት ሲመርጥ ታማኝ መሆኑን ኣይቶ ነው፤ በእርግጥም ሙሴ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ሕዝብ የታመነ ነበረ፤
ሙሴ የንጉሥ ልጅ ከመባል ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን፣ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍን፣ በኃጢኣት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ መሰደድን በመምረጥ ታማኝነቱን በተግባር ያረጋገጠ ነበር፤
በዚህም እግዚአብሔር ሙሴን ኣምኖ በሕዝቡ ላይ ሾሞታል፤ እሱም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ኃላፊነቱን ተወጥቶኣል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ኣስተምህሮ ሳይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች ኣሰራር ውሱን ሕፀፅ ባይጠፋም፣ መዓዛ መንፈስ ቅዱስ ኣይለያትምና ኣሁንም ዓለም መታመንን ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች ትጠብቃለች፤
ከዚህ ኣኳያ ይህ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን መታመን እንዲኖር ኣብዝቶ የመስራትና የማሰራት ግዴታና መለኮታዊ ኃላፊነት ኣለበት፤
በዓለ መክሊቶቹ ‹‹ባእ ውስተ ፍሥሓሁ ለእግዚእከ›› ተብለው የተመሰገኑበትና የተሸለሙበት ዋና ምክንያት ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ የምናውቀውና በየቀኑ የምናነበው ነው፡፡
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
ጉባኤ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት የተሳሳተ ሲኖር ለማስተካከል፤ የተዛባ ሲኖር ለማቅናት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤
ከዚህ ኣንጻር በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሰው ኃይል ኣስተዳደራችን፣ የሃብት ኣጠባበቃችን እንዲሁም የምእመናን ኣያያዛችንና ሓዋርያዊ ተልእኮኣችን ለዘመኑ የማይመጥን እንደሆነ በስፋት እየተወሳ ነው፤
አስወቃሽ ምልክቶችም እየታዩ ነውና ያሉብንን የኣሰራር ክፍተቶችን በሚገባ ፈትሸን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘላቂ መፍትሔን በማስቀመጥ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት በተለይም በኣፍሪካና በላቲን ኣሜሪካ ያሉ ዕድሎችን በታቀደና በተጠናከረ ሁኔታ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ይህ ጉባኤ ማየት ኣለበት፣
ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተልእኮ በኣግባቡ መወጣት የሚችለው በሃገር ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሕዝባችን ካጋጠመው ያልተቋረጠ መከራና ጭንቀት ያርፍ ዘንድ፤ ለሰላም ከመጸለይ ባሻገር የማግባባት፣ የማስታረቅና የማስማማት ስራ ከኛ ይጠበቃልና በዚህም መወያየት ይኖርብናል፤ ለባለ ድርሻ ኣካላትም የሰላምን ጥሪ ማስተላለፍ ይገባናል፡፡
በመጨረሻም
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከጥቅምት ዓሥራ ሁለት ቀን ጀምሮ የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖደስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን ለኦርቶዶክስ ምእመናን እናበስራለን ፡፡
እግዚአብሔር የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!
ኣባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘኣኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ - ኢትዮጵያ

ተዛማጅ

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል

ዜና

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል

21 Oct 2026

የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡የብፁዕ ሊቀጳጳሱ ጸሎተ ፍትሐት ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ከቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ጋር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ መሪነት የሚከናወን ሲሆን ፤ የሌሊቱ ሥርዓተ ፍትሐት እና አደራረስ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቀጥሎ የሚከናወን ይሆናል፡፡የብፁዕ አቡነ ሉቃስ ግብአተ መሬት ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቅዳሴ በኋላ የሚፈጸም መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ
የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

ዜና

የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

19 Oct 2026

የጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪካዊ የልማትና የዕድገት ጉዞ የሚያንጸባርቅ፥ በቴክኖሎጂ አደረጃጀቱና በግንባታ ጥራቱ የላቀ ዘመናዊ ቅርስ ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ። ዘጋቢ ሰላም አምባዬ (#EOTCTV ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለዘመናት ሲገነባ የቆየውን ''ጽርሐ ተዋሕዶ ዓለም ዓቀፍ የጉባኤ ማዕከል ተብሎ የተሰየመው ዘመናዊ የጉባኤ ማዕከል ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ተመርቋል። በምረቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የዓለም ዓቀፉ የጉባኤ ማዕከል ግንባታ ለፍጻሜው ሊበቃ የቻለው በየዘመናቱ የተተኩ ቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ባደረጉት ያልተቋረጠ ክትትልና አባታዊ አመራር መሆኑን በሕንጻው ምርቃት ላይ በስፋት ተገልጿል ። በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ፣ ተቋማዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታስቦ የተገነባ ሲሆን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛና አስቸኳይ ጉባኤያትን፣ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን፣ የእህት አብያተ ክርስቲያናትንና የዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ተቋማት የጋራ ስብሰባዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳለው ገልጸዋል ። ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በንግግራቸው አዳራሹ ከስብሰባ አዳራሽነቱ ባሻገር ለልዩ ልዩ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች የሚውሉ ዘመናዊ ቢሮዎችን፣ ያካተተ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፤ ለተኪው ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ቅርስ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም አክለዋል ። በተጨማሪም የጉባኤው ማእከል ከስብሰባ አዳራሽነት ባሻገር ለልዩ መንፈሳዊ፥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች የሚውሉ ዘመናዊ ቢሮዎችን፥ አነስተኛ የስብሰባ ክፍሎች እና ጥናታዊ ሲምፖዚየሞች የሚካሄዱባቸውን መድረኮችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን ያካተተ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ። የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/ See less

ተጨማሪ ያንብቡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡

ዜና

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡

19 Oct 2026

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎበኙ፡፡ መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተገነባው አዲሱ ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ሁለገብ የሰብሰባ ማዕከል የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ማዕከል ነው፡፡ ይህን ግዙፍ ሕንጻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ጥራትና ውበት የተላበሰው ሕንጻ በሚገባ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ በሕንጻው ዙሪያ በቂ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንዲኖር፥ ቅጽረ ግቢው ቤተ ክርስቲያንን በሚገልጽ ሥነ ጥበብ እንዲያጌጥ ተደርጎ የተሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በምሕንድስና ባለሙያዎቹ እንደተገለጸው ዓለም አቀፍ ሁለገብ ሕንጻ ከ2‚260 በላይ ተሰብሳቢዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዳራሽ፥ ሌሎች አነስተኛ የስብሰባና የሥልጠና አዳራሾች፣ ከአንድ መቶ በላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን የሚይዝ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ፥ ሙዚየምና ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ ቢሮዎች፣ ዘመናዊ ሬስቶራንትና ለሌሎችም አገልግሎት የሚሰጥ ክፍሎችን የያዘ ተገልጿል፡፡ አዲሱን ሁለገብ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ጥቅምት ፩ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም የሚመረቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/ See less

ተጨማሪ ያንብቡ